
ነሐሴ 23፣ 2017 (August 29, 2025)
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከንቱ ድካም በአሜሪካ
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ልዑካን ወደ ሰሜን አሜሪካ ተጉዘው ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን የማነጋገር ከንቱ ልፋት ይመለከታል ይህ መግለጫ። የምክክር ኮሚሽኑ በዐዋጅ ቁጥር 1265/24 ሲቋቋም፣ ራዕዩ “እጅግ መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ሀገራዊ መግባባት ተፈጥሮ ማየት” ነው ብሎ ነበር።እሴቶቹን ሲዘረዝር ደግሞ፣ “አካታችና አሳታፊነት፣ገለልተኛነት፣ግልጽነትና ተጠያቂነት፣ብቃትና ሙያተኝነት፣አጋርነትና ትብብር፣ የሕግ የበለይነት፣ ተዓማኒነትና ቅቡልነት” ናቸው ብሎ ነበር።
በዛሬዋ ኢትዮጵያ ውስጥ እጅግ መሠረታዊ የሆኑት ጉዳዮች ምንድን ናቸው ብለን ስንጠይቅ፣ በማይታበል ደረጃ የዜጎች የህይወት ዋስትና ማግኘት፣ በሀገሪቱ የሠላም መስፈን፣ የጦርነቶች መቆም፣ የዜጎች በነፃነት መነቀሳቀስና ሃሳባቸውን መግለጽ መቻል፣ የሕግ የበለይነት መኖር፣ የዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር፣ እንዲሁም ሠርተውና አምርተው ራሳቸውንና ቤተሰባችውን ማኖር ...” ሆነው እናገኛቸዋለን። እነዚህን መሠረታዊ ጉዳዮች በተመለከተና ሀገሪቱን እያመሰቃቀለ ስላለው ዘረኝነትና፣ኢትዮጵያ ዉስጥ ይህንን በዘረኝነት ላይ የተመሰረተ ሥርዓትን ስለተከለው ሕገ-መንግሥት መሻሻል ኮሚሽኑ ትንፍሽ ብሎ ያውቃል? የምክክር ኮሚሽኑ በሦስት ዓመት እድሜው ውስጥ የሰራቸው ስራዎች ምንድናቸው? ጦርነቶች እንዲቆሙ ጠይቋል? የዜጎች ህይወት በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች በየዕለቱ እንደቅጠል እየረገፈ፣ ደማቸውም እንደጎርፍ ሲፈስ፣ ይህንን ግፍና ዕልቂት አውግዟል? ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ የምክር ቤት አባላት ጭምር፣ እንዲሁም እልፍ ዐዕላፍ ንፁሃን ዜጎች ከየቤታቸውና ከሥራ ቦታም፣ ከመንገድም እየታፈሱና እየታፈኑ ሲታሰሩ፣ አንዳንዶች ጭራሽ ደብዛቸው ሲጠፋ፣ ይህን መረን የለቀቀ ሕገ-ወጥነቱን መንግሥት እንዲያቆም ጠይቋልን? ለመሆኑ የምክክር ኮሚሽኑ በዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ውስጥ የሕግ የበላይነት አለ ብሎ ያምን ይሆን?የትኞቹን እሴቶችን ነው የሚጠብቀው?
ሁለተኛ፣የምክክር ኮሚሺኑ እስከዛሬ እያወያየ ያለው እነማንን ነው? በየሥፍራው ገዥው ብልጽግና ፓርቲ እያሰባሰበ የሚያመጣለትን፣ ማለትም ለገዥዎቹ ታማኝ የሆኑትን፣ አጀንዳ እንዲሰጡ ቅድመ ዝግጅት ተደርጎላቸው የሚሰበሰቡለትን እኮ ነው የሚያነጋግረው? የትኞቹ ናቸው “ባለድርሻ” ሊባሉ የሚችሉት? ስለ ተሰብሳቢዎችም ሆነ ስለ አካሄዱ ሌሎችንም ጉዳዮች በሚመለከት፣ ሀገር ውስጥ በሠላማዊ መንገድ በህጋዊነት በሚንቀሳቀሱና እስከዛሬ ነፃነታቸውን በጠበቁ፣ የፖለቲካ ድርጅቶች ተደጋግሞ ተገልጾላቸውም “ጆሮ ዳባ ልበስ” ብለው የደመ-ነፍስ ጉዟቸውን ቀጥለዋል፣ ወደ ሰሜን አሜሪካም መጥተዋል።
የኢትዮጵያ ሁለቱ ክልሎች፣ የአማራ ክልልና ከፊል የኦሮሚያ ክልል፣ የጦርነት አውድማዎች ሆነዋል። በተለይ የአማራ ህዝብ የኅልውና አደጋ ውስጥ ስለገባ፣ እንደ ህዝብ “አጠፋዋለሁ” ብሎ የዛተበትንና ጦር ያዘመተበትን፣ዘረኛና አምባገነናዊ የብልጽግና መንግሥት እንደ ህዝብ መሣሪያ አንስቶ ላለመጥፋት እየታገለ ነው። ኦሮሚያም ውስጥ የፖለቲካ ጥያቄ ስላላቸው ብልጽግናን መሳሪያ አንስቶ የሚታገል ኃይል አለ። ትግራይ ከአውዳሚው የሰሜኑ ጦርነት ሳታገግም፣ ዛሬም ሠላም እንዳጣችና ህዝቡም ከፍተኛ ችግር ውስጥ ገብቶ፣እየማቀቀ ይገኛል። ወትሮ ደቡብ ኢትዮጵያ ይባል የነበረውና ዛሬ ብልጽግና እየከፋፈለ ያለው አካባቢም እየታመሰ ነው። የአዲስ አበባን ሕዝብ መንግሥት ራሱ እያሸበረው ይገኛል። ከአዲስ አበባ ውጭ ደግሞ መንግሥት በግልጽና በስውር ባሰማራቸው ሃይሎች፣ እንዱሁም በአንዳንድ ሥርዓት በሌላቸው የታጠቁ ቡድኖች ከነፍስ ማጥፋት ጀምሮ፣በሕብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ ጉዳትና ምስቅልቅል እያደረሱ ነው።
ታዲያ የቅራኔዎች ከፍተኛ መገለጫ የሆነውን፣መንግሥትን በመሣሪያ ጭምር የመፋለም፣ቅድሚያ የሚጠይቅ ጉዳይ ችላ ብሎ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ምን ዓይነት ድርድር፣ ምንስ ዓይነት ምክክር፣ማድረግ ይቻላል? ልፋታችሁ ከንቱና ውጤት አልባም ነው የሚሆነው እንላለን። የችግሩ ዋና ዋና ባለቤቶች በሌሉበት መድረክ ላይ የኢትዮጵያን ችግር መፍታት አይቻልምና፣ ኮሚሺኑ ከኢትዮጵያ ውጭ የሚያደርገውን ጉዞ ከማቀዱ በፊት፣በአገራዊ ምክክር ሂደቱ ውስጥ አገር ውስጥ የሚገኙ ዋና ዋናዎቹ የችግሩ ባለቤቶችና እንዲሁም የተለያዩ የሲቪክ፣ የፖለቲካና ማህበራዊ ባለድርሻዎች መካተታቸውን ማረጋገጥ ይኖርበታል፣ ደግሞም ኢትዮጵያ ውስጥ አገራዊ ጉባኤ ከመካሄዱ በፊት ጦርነት ቆሞ ሰላምና መረጋጋት ሊኖር ይገባል።
በትጥቅ እየተፋለሙ ያሉትን ሃይሎች በሚመለከት፣ ኮሚሽኑ በድረ-ገጹ ላይ፣ “ ... መንግሥትን ጨምሮ፣ በግጭት ላይ ያሉ ሁሉም ወገኖች፣ ግጭቶቻቸውን በተለየዩ አማራጮች ፈትተው፣ አጀንዳቸውን ወደ ምክክሩ ጠረጴዛ በማምጣት እንዲሳተፉ፣ ኮሚሽኑ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ እየሠራ ነው” ይላል።(ሠረዝ የኛ ነው) ለመሆኑ ኮሚሽኑን ያቋቋመውና ኮሚሽኑም በቅንነት እያገለገለው ያለው የብልጽግና መንግሥት፣ሁሉንም የሀገሪቱን የፖለቲካ ችግሮች በጦርነት ብቻ ለመፍታት እንደሚጥር አያውቅም ማለት ይቸግረናል። ስለዚህ ብልጽግና ተቃዋሚዎቹን በጦርነት ከደመሰሰ በኋላ “አጀንዳቸውን ያምጡ” ማለቱ ይሆን? መደምሰሰ ከቻለ፣ የራሱን ፍላጎት እንደሚጭን ተስኗቸው ይሆን? ኮሚሽኑ፣ የምክክር ሥራውን በተመለከተ፣ “የሕግ የበላይነትን ባከበረ መልኩ ነው የሚካሄደው” ይልና ስለሆነም፣ ማንኛውም የመሣሪያ ትግል እያካሄደ ያለ ሃይል “ወደ ምክክሩ ሲመጣ፣ የሃይል አማራጮች ዝግ ተደርገው መሆን ይኖርባቸዋል” ይላላ። ገዥው ብልጽግናም እኮ የሚለው፣ “በቅድሚያ መሣሪያችሁን ደርድሩልኝና ሁላችሁንም ያለምንም ችግር አጠፋችኋለሁ” እያለ ያለው?
እሳት ካየው ምን ለየው? ስለዚህ በኮሚሽኑ ውስጥ እንደ ግለሰብ የምናከብራችሁ ሰዎች ብትኖሩበትም፣አሁን በምታደርጉት አምባገነኑን ፀረ-ሕዝብ መንግሥት የማገልገል ተግባር፣ ኢትዮጵያን እየጎዳችሁ እንዳላችሁ፣ለማመን ተገደናል።
ፈጣሪ አምላክ ኢትዮጵያንና ህዝብዋን ይታደግ!!
መላው ህዝብ ለሀገሩ ህልውና፣እናም ለነፃነቱ ለመታገል በአንድነት ይነሳ!!
የኢትዮጵያውያን ትብብር ንቅናቄ!!!
Unity
Promoting collaboration among Ethiopians in diaspora.
Support
Action
info@ethiosolidaritymovement.org
+1 (202) 754-5328
© 2025. All rights reserved.